Sunday, October 7, 2018

የካቲት 24 1988 አ.ም.

ጉዋደኛዬ 

ያደኩበት ሰፈር ልጅ የሆነው የዛሬው የቅርብ ጉዋደኛዬ የጉዋደኞቼም ጉዋደኛ ጌታሁን በምህንድስና ስራው ወደ ጅማ ተመድቦ ከመጣ በሁዋላ በጅጤሳ የማሳልፈው ከንባብና ከትምህርትጋ ትንቅንቅ የበረከተበት ሂወት በመጠኑ ተለውጧል :: ጌታሁን የተዋበ ቀለም ጨመረበት:: በተወሰነ መልኩ አንፃራዊ ምቾት አከለበት:: እኔ በተማሪነት ሂወት ውስጥ ያለሁ ነኝና ብዙ ግዜ ኪሴ ንዋይ-አልቦ  የነበር ቢሆንም በሥራ አለም ላይ ካለው ጉዋደኛዬ ጌታሁን ጋ በማሳልፋቸው ግዜያት ሁሉ እሱ ያለስስት እያወጣ አብረን እንዝናናለን:: በሳምንቱ መጨረሻ ቅዳሜና እሁድ ከጤና ሳይንሱ ግቢ በሩጫ በሚባል ፍጥነት ወጥቼ ጌታሁን ወደሚኖርበት አፓርታማ እሄዳለሁ:: ይህ ጅማ ከተማ መሃል ከባንክ ቤቱ አሻጋሪ የቆመው የመኖሪያ ህንፃ ውስጡ ዘመናዊ የሆኑ ቁሳቁሶች (Furnitures ) አሉት:: የቤቱም አሰራር ዘመናዊ ነው:: ሳሎኑ: መኝታ ቤቱ: መፀዳጃ  ቤቱ ሁሉ እኔ ዘወትር ከምኖርበት ዶርም እጅግ የተሻለ ብቻ ሳይሆን የተራራቀ  ነው:: ታድያ የሳምንቱ መጨረሻ ላይ ወደዚህ ቤት ስመጣ ከፍተኛ ነፃነትና መለቀቅ ይሰማኛል:: የሰውነቴ ሴሎች ይፍታታሉ:: አንዳንዴ እዚህ ቤት ውስጥ በንባብና በጥናት ተግቼ  አድራለሁ:: ጌታሁን እኔን ለማመቻቸትና  ዘና ለማድረግ አይቦዝንም :: በተደጋጋሚ  አለ ወደተባለ ምግብ ቤት በመሄድ ጥሩ እራት ከጋበዘኝ በሁዋላ ቢራ ውይም ወይን ጠጅ  እየጠጣን የተለያዩ ጉዳዮችን ስናወጋ በሙዚቃም ስንዝናና እናመሻለን:: እንዳንዴም ፓርቲና ዳንኪራ ያሉባቸው ቦታዎች እንሄዳለን:: በተለይ የ 1988 አምን የገና በዓል ከጤና ሳይንሱ በስተጀርባ ወደ ጅማ ከተማ መግቢያ ላይ በሚገኘው ባላምባራስ ሜጫ ሆቴል እንዴት እንዳሳለፍነው አይረሳኝም:: ያ ቤት የገና ለት በተማሪዎችና ተማሪዎችን ብለው በመጡ የከተማው ወጣቶችና  ቡና ነጋዴዎች  ጥቅጥቅ ብሎ ነበር::  የዳዊት መለሰ "እኔ አልቻልኩም መጋየት አቅቶኛል" የ UB -40 " ሬድ  ሬድ ዋይን " የላፎንቴኖች  "ተው አምላኬ አለሁ በለኝ" ሙዚቃዎች በዳንስ የታበደባቸው ነበሩ........

Sunday, September 23, 2018

ታህሳስ 22 1988 አ.ም. (ጃኑዋሪ 1፣ 1996 እ.ኤ.አ.)

ሀበሻ ላልሆኑ በአብዛኛው የዓለም ክፍል ለሚኖሩ ስዎች ዛሬ የአዲስ ዓመት የመጀመሪያ ቀን ነው:: 1995ን ጨርሰው ወደ 1996 ገቡ:: መልካም አዲስ ዓመት ብያለሁ:: እኔ ግን ይህን ቀን የማስታውሰው የአእምሮ ሕክምና (psychiatry ) ትምህርት የሁለተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን በመሆኑ ብቻ ነው:: ያ የለፈው የታህሳስ መጀመሪያ የፈተና ሰሞን አለፈ:: እኔም ፈተናዬን ተፈተንኩ:: ነገር ግን ለትውስታ የሚሆን አንድም ነጥብ ሳላሰፍር እንደተፈተንኩ ላጭር ረፍት ወደ አዲስ አበባ ሂጄ ነበር:: ባለፈው ሰኞ ወደ ጅማ ተመለስኩ:: የአእምሮ ሕክምና ትምህርትም በበነጋው ተጀመረ:: በቅጡ ማንበብ ባልጀምርም ትምህርቱን ወድጀዋለሁ:: ከሕክምና ትምህርቶች ሁሉ አንደኛ የምወደው እሱ ነው ብዬ ደፍሬ መናገር ባልችልም በትምህርቱ ክፍለግዜ ስለሰዎች ባህሪ ፣ አንዲሁም ስለ psychoanalysis የምናደጋቸውን ውይይቶች በጣም ተመስጬባቸዋለሁ:: ምናልባት ቤተሰብ ጋ እረፍት አድርጌ ገና መምጣቴ ስለሆነና ያዕምሮዬም ጤና ጥሩ ስለሆነ ጥሩ ተሰምቶኝ ይሆናል እንዲህ ያልኩት:: 


የካቲት  17 1988 አ.ም. እሁድ 

የአራተኛ አመት የህክምና ተማሪ የሆነው ክንፈ ዛሬ ሞተ:: ራሱን በስቅላት አጠፋ:: በማደሪያ ክፍሉ ባለ ሎከር ውስጥ በኤሌትሪክ ገመድ ተሰቅሎ ተገኘ:: ምን ማለት እንዳለብኝ አላውቅም:: እጅግ ጥልቅ የሆነ ሃዘን እየተሰማኝ ነው:: የመሞቱን ወሬ ከሰማሁ በሁዋላ ጉዋደኞቼን አግኝቼ አስከማረጋግጥ አላመንኩም ነበር:: እንደኔና እንደአብዛኞቹ ተማሪዎች ከድሀ ቤተሰብ የተወለደና የወደፊት ሂወቱን ብሩህ ለማድረግ የሚፍጨረጨር ምስኪን  ዜጋ ነበር:: ራሱን አጠፋ? ለምን? ኦ አንተ አግዚአብሔር ወጀቡን አረጋጋው: ቀሪዎቻችንን እንዲህ አናደርግ ዘንድ ጠብቀን! አሜን!

የለም! ገና አልጨረስኩም:: በዚህ ጉዳይ የምለው ተጨማሪ ነገር አለ:: ስለክንፈ ሳይሆን ስለራሴ:: እንዲዚህ አይነትና መሰል ሁኔታዎች ከዚህ በፊት ሲከሰቱ ስለክስተቱ ብቻ ሳይሆን ስለራሴም በጥልቅ  አስባለሁ:: አሁን ከምሽቱ አምስት ሰዓት ነው:: እኔም ሆንኩ የክንፈን ሞት የሰሙ የጤና ሳይንሱ ተማሪዎች በሙሉ ያልተረጋጋ ስሜት ውስጥ ነን:: አንዳንዶቹ የመኝታ ክፍል ተጋሪዎቼ 
ተኝተዋል:: እንደክንፈ አይነት አሟሟት እንደማልሞት አርግጠኛ መሆን አሰኘኝ ::  ሁልግዜ ችግር እንዳለብኝ እያሰብኩ በኑሮም እነጫነጫለሁ:: አሁን ግን ሳስበው ያ ሁሉ እውነት አይደለም:: ሌሎች  መፍትሄ የሌለው ከባድ ችግር ያለባቸው ሰዎች አሉ ማለት ነው:: 

ዛሬ እጀግ ብራ የሆነና ነፋሻ ያማረ መልካም እሁድ ቀን ሆኖ ነው የዋለው:: ክንፈም በመፅሃፍት ቤቱ ውስጥ በትጋት ሲያጠና ነበር- እስከ ምሳ ሰዓት ድረስ:: ከዚያ ቀጥሎ ወደ ማደሪያ ክፍሉ በመሄድ ራሱን አጠፋ! ብዙ ግዜ ለብቻው የሚራመድ : ብዙ የማይናገርና ብዙም ለትምህርቱ ደንታ የሌለው የሚመስል ልጅ ነበር:: ተማሪ ራሱን ሲያጠፋ በ ጤና ሳይንሱ ታሪክ ክንፈ የመጀመ ሪያው ነው::

ፍርሃት ፍርሃት አለኝ:: ምንን  እንደምፈራ ግን አላውቅም::  መንግስቱ ክንፈን ይቀርበው ነበር:: አሁን መንግስቱ የት ነው ያለው? ሬሳውን አጅቦ ወደ ክንፈ አገር እንድብር ሄዷል መሰለኝ::

እዚግህ ላይ ይብቃኝ መሰለኝ መፃፉ:: 10 ሚሊግራም  ዲያዜፓም ያስፈልገኛል:: አለዚያ እንቅልፍ ላይወስደኝ  ይችላል:: ወይስ አልውሰድ? ትንሽ ልጠብቅ እስቲ ........

ማስታወሻ: በዚህ ቀን ፅሁፌን ከጨረስኩ  በሁዋላ በድንገት ሳላውቀው እንቅልፍ ወሰደኝ:: ያዘጋጀሁትን ዲያዜፓም ታብሌት አልወሰድኩትም Wednesday, September 12, 2018

የፈተና ሰሞን 

ማክሰኞ ታህሳስ ሁለት  ቀን 1988 ዓም 

ዛሬ ምሽት ላይ ዝናብ ጣለ:: በጋራ መኝታ ቤታችን ውስጥ የሚኖሩ ሁሉ ከኔና ከመንጌ በስተቀር ነገ የየተመደቡበትን ክፍል ፈተና ያጠናቅቃሉ:: መንጌ የውስጥ ደዌ ትምህርት ፈተና ሐሙስ የሚያጠናቅቅ ሲሆን እንደ ዕድል ሆኖ እኔ ግን ለመፈተን የመጨረሻው የዶርሙ አባል በመሆን አርብ የውስጥ ደዌ ትምህርቴን እፈተናለሁ:: በህክምና ትምህርት ውስጥ እንዲህ ያሉ የምጥና የመከራ ቀናት ለኔ አዲስ አይደሉም ነገር ግን የዶርም ተጋሪዎቼ በሙሉ ፈተናቸውን ጨርሰው እያየሁ እንዴት አዘልቀዋለሁ! ከባድ ነው የሚሆንብኝ:: ከኔና ከመንጌ በቀር ሌሎቹ ነገ የሚፈተኑት በሙሉ የማንበብ ፍጥነታቸውን ቀንሰው ለማይቀረው ፈተና ሃሳባቸውንና አእምሮአቸውን በማረጋጋጋት ላይ ናቸው:: የመጨረሻው ተፈታኝ በመሆኔ ከፋኝ:: ብቸኝነት ተሰማኝ:: ዛሬ ከሰዓት በሁዋላም የጎሰጎስኩት የጫት ምርት አላመረቀነኝም:: ፀጥ ግን አድርጎኛል:: የመኝታ ክፍል ተጋሪ የሆኑትና የቅርብ ጉዋደኞቼ  በሙሉ በአካል አጠገቤ ቢሆኑም በውስጤ የተፈጠረውን የብቸኝነት  ስሜት ሊያስታግሱት አልቻሉም:: ጭንቀትና የስሜት አዘቅት እየተፈራረቁብኝ ነው......


ሐሙስ ታህሳስ አራት  ቀን 1988 ዓም 

አሁን ከቀኑ ስድስት ሰዓት ነው:: መኝታ ቤታችን ውስጥ ካለው ግዙፍና ባዶ ጠረጴዛ ፊት ተቀምጫለሁ:: ቤተማርያም ትናንት ፈተናውን ያጠናቀቀ በመሆኑ ዛሬ ለሽ ብሎ አልጋው ላይ ተኝቷል ::በዚህ ሰዓት መንጌ ምናልባት የርሱን ፈተና ጨርሶ ይሆናል::  ገና አልመጣም:: ከዚህ መኝታ ክፍል እኔ ብቻ ነገ እፈተናለሁ:: ከጭ ንቀቱና ከስሜት አዘቅቱ ላይ ዛሬ ድካም ታክሎበታል-ጎሽ! ደ ብተርም ሆነ መፅሐፍ ማየት አስጠልቶኛል....

በነገራችን ላይ ዛሬ ጠዋት ከቤት በፖስታ የተላከልኝን  ወርሓዊ ሃምሳ ብር ጅማ ፖስታ ቤት በመሄድ በጠዋት ከተቀበልኩ በሁዋላ የነበሩብኝን የሱቅ ዱቤዎች ከፍዬ ባሁኑ ሰዓት ከወጪ  ቀሪ ምንም የለኝም:: ወደፖስታ ቤት ከመሄዴ በፊት በነበርኩበት አቁዋም ላይ ነኝ :: አሁን ያማረኝ አጭር የመኝታ ግዜ ውይንም ናፕ ነው፣ ከተቻለ :: ስህተት መሆኑን ባውቅም በተደጋጋሚ ፈተናዬ ከባድ ይሆናል ብዬ ማሰቤን መተው አልቻልኩም......

Saturday, December 23, 2017

ህዳር 25 1988 አ.ም.

በዚህ ቀን ጠዋት የኔ ቡድን ያልጋ ዙሪያ ትምህርት (bedside) የነበረው ሲሆን አንዱም የቡድኑ አባል ትምህርቱ ጠዋት እንደሆነ ስላልነገረኝ ሳልገኝ ቀረሁ:: አመለጠኝ::  ለኔ ፕሮግራሙ ከሰአት በሁዋላ የሚካሄድ  ነበር የመሰለኝ:: እንደዚህ መቅረት  በጣም በጣም ነው የሚከብደኝ:: ጠዋት እኔ ተረጋግቼ አገር ደህና ብዬ ስረማመድ አምስት ሰዓት ተኩል ገደማ ተቧዳኞቼ በእውቀት በልፅገው ሲወጡ አየሁዋቸው:: ያለኔ መኖር  ይህ በመሆኑ ከመጠን ባለፈ ተበሳጨሁ : ሴራ መሰለኝ:: ሁሉንም  ለተወሰኑ ሰአታት ጠላሁዋቸው:: ክፉዎች!

በዚህ ቀን ምሽት ላይ በጣለው ዶፍ የቀላቀለ ዝናብ ምክንያት የኤሌክትሪክ አገልግሎት በመቁዋረጡና ለማንበብ የሚረዳ የመብራት አገልግሎት በመጥፋቱ የተከሰተውን ሰበብ በመንተራስ የቅርብ ጉዋደኞቼና የአስተሳሰብ ተጋሪዎቼ ከሆኑት አብይና አብርሃም ጋር በመሆን ከጤና ሳይንሱ ወረድ ብላ ከምትገኘው ቆጪ ሰፈር በመጠጥ ለመዝናናት ወረድን::  ሌላ ጉዋደኛችን ተከራይቶ ከሚኖርባት ሁለት ሜትር በሁለት ሜትር የምትሆን ትንሽ የኪራይ ቤት ውስጥ መሬት ላይ ተቀምጠን ከዚያው አካባቢ ያስገዛነውን ጠጅ እየጠጣንና የፍልስፍና ድባብ የተላበሰ ወግ እየጠረቅን አመሸን:: እኔ መቼም ከዚህ በፊት እንዳልኩት ከምወዳቸውና ሃሳብ ከሚጋሩኝ ጉዋደኞቼ ጋር የማሳልፈውን ግዜ በፍቅር ነው የማጣጥመውና  የምወደው:: ምንም እናርግ ምን ወይም ምንም አናርግ አያገባኝም ነገር ግን ከነዚህ ጉዋደኞቼጋ መሆንና ግዜውን አብሮ ማሳለፉ ብቻውን የሚሰጠኝ ደስታ አለ::  በዚያች እስር ቤት በምታህል ትንሽ ክፍል ቤት ውስጥ  በሻማ ብርሃን እየተያየን: ጠጃችንን እየጠጣንና በየተራ ምናባችን የሰነቀውን ፍልስፍናዊ ሃሳቦች እየተካፈልን እንዲሁም እያካፈልን እስከ ምሽቱ አምስት ሰዓት ቆየን::  ወደ ጤና ሳይንሱ ስንመለስ ደጁ በደማቅ ጨረቃ የተዋበ ነበር::  ጨረቃ ድምቡል ቦቃ.....


በበነጋው ወደተለመደ ትምህርት የተሞላ ባህር ውስጥ ገባሁ:: የውስጥ ደዌ ሕክምና ፈተና እየተቃረበ ስለነበር ትከሻዬን መክበድ አስቀድሞ ጀምሮኛል...........:: ትከሻ መክበድ ብቻ ሳይሆን ፈተና ሲደርስ አይኔም መርገብገብ ይጀምራል:: ግን ይህን ሁሉ ስለለመድኩት ምንም አይመስለኝም:: አንዳንዴ አንዳውም በዚህ ሁሉ ርካታ አልባ የህክምና ትምህርት የንባብ ሂወት ውስጥ እየተሰቃየሁ ይሆን እንዴ? ብዬ አስባለሁ:: እየተሰቃየሁ ቢሆን በውነቱ ላውቀው አልችልም:: የስሜት ህዋሳቶቼና የስሜት መሰማት አቅሜ ክፉኛ ስለቀነሱ አእምሮዬ የተለያዩ አጋጣሚዎችን ባንድ አይነት ሁኔታ መቀበል ከጀመረ ቆየ....

Sunday, October 22, 2017ጥቅምት 19 1988 አ.ም.

የውስጥ ደዌ ሕክምና (Internal Medicine) በእውነትም ሰፊ እጅግ በጣም ሰፊ ነው:: በዚህም የተነሳ አሁን ያለሁበት የተግባር ልምምድ ፈታኝ ነው:: ብዙ ብዙ ብዙ እጅግ በጣም ብዙ ማንበብ ይጠይቃል:: ማንበብ ብቻ ሳይሆን ብዙ መጠየቅን ይጠይቃል:: እያንዳንዱ በሽታ ለምን አንደመጣ ከየት እንደመጣ እንዴት እንደመጣ መቸ እንደሚያበቃ በምን እንደሚያበቃ ምን እንደሚያስከትል  እና ሌሎችም እልፍ ጥያቄዎች መመለስ አለባቸው :: እንደ የውስጥ ደዌ ሕክምና ተማሪነቴ እንዚህን ሁሉ ጥያቄዎች በሰኮንድ በሚቆጠር ቅፅበት በአእምሮዬ ውስጥ ፈጥሬ መልሱንም መመለስ ይጠበቅብኛል::  ይህ ግን በተግባር ቀላል እንደማይሆን ግልፅ ነው:: የቻልኩትን ያህል እሞክራለሁ:: የቻሉትን መሞከር ጥሩ ተግባር ቢሆንም ዶክተር ጴጥሮስ በሚጠይቅ ግዜ ከላይ በተጠቀሰው መልኩ አውቆ አለመገኘት ተስፋ አስቆራጭ ነው:: ለአሸማቃቂ ትግሳፅ ይዳርጋል::

እያንዳንዱን በሽታ ከስሩ ጀምሮ ለማንበብና ለማስታወስ ከሚገመተው በላይ ግዜ ስለሚወስድ ብዙ ግዜ መሸምደድ ያስፈልጋል:: ሽምደዳ አጭሩ መንገድ (Shortcut) የሆነበት ፊልድ ሕክምና ብቻ ይመስለኛል::

የህክምና እውቀታችን ከሚገመግምባቸው የዘወትር መድረኮች አንዱ ያልጋ ዙሪያ ውይይት (Bed  Side) ነው:: በዚህ በበሽተኛው ዙሪያ ቆመን በምናደርገው ውይይት ከመካከላችን አንድ የህክምና ተማሪ ከተመደቡለት ህሙማን ሰለ አንዱ ዝርዝር ሁኔታ ለአስተማሪው ዶክተርና ለቡድኑ አባላት ያቀርባል::  አስተማሪው በርካታ ጥያቄዎች ይጠይቃል:: አብላጫው ጥያቄ ላቅራቢው ቢሆንም  ሁሉም የቡድኑ አባል ቢያንስ አንድ ጥያቄ ይደርሰዋል:: ሁሉም ያቅራቢውን ሐተታ ከሰማ በሁዋላ በፍጥነት በማሰብ ጥያቄ ለመመለስ መዘጋጀት አለበት:: አላውቀውም ማለት ቢቻልም ደጋግሞ ግን አላውቀውም ማለት ከላይ እንዳልኩት ለአሸማቃቂ ታግሳፅ የሚዳርግ ነው::


ለምሳሌ ዛሬ ጠዋት አንድ AGN (Acute Glomerulonephritis) ኬዝ ላይ Bed  Side ነበረን: ከዶክተር ጴጥሮስ ጋር:: ባጠቃላይ ጥሩ አልነበረም:: ( ማለትም ዶክተር ጴጥሮስ ሁላችንንም ገስፆናል) ማለት ነው::  ከሰዓት ደሞ Management Session ነበረን:: ይህ እንደ Bed  Side አይነት ቢሆንም በሽተኛው በሌለበት ክላስ ሩም ውስጥ የሚካሄድ ጠለቅ ያለ ትምህርት ነው:: ኬዙ Diabetic Ketoacidosis, Hypoglycemia ና Hyperosmolar coma ነበር:: እጅግ የሚያደክም ከሰዓት ነበር:: በዚህ የተነሳ ምሽቱን ከማንበብ ቦዘንኩ:: ለነገ መነበብ የነበረባቸውን Anemia ና Bone & joint tuberculosis ሳላነብ አሸለብኩ:: 

Sunday, July 9, 2017

ማክሰኞ ጥቅምት 13 1988 አ.ም.


ህክምና ትምህርት ሁሉ ስፋት ግዝፈትና ጥልቀት ዋና መገለጫ የውስጥ ደዌ ሕክምና (Internal Medicine) ነው:: የ Internal Medicine ሁለተኛ ዙር ትምህርታችንን ዛሬ ከዶክተር ጴጥሮስ ጋር በተደረገ የህሙማን ጉብኝት (Round) ጀመርን:: ባለፈው ሳምንት ደስ ባላለኝ መልኩ የተጠናቀቀው የቀዶ ሕክምና (Surgery) ትምህርት ያዞረው ናላዬ ወደነበረበት ገና አልተመለሰም:: ስለዚህም የዛሬውን Round በግማሽ አቅሌ ነው የተከታተልኩት:: ኢንተርኞቹ የሕሙማኖችን የምርመራ ውጤት እንዲሁም የህክምና ዝርዝር (Management Plan) ለዶክተር ጴጥሮስ ሲገልፁለትና በጉዳዩ ላይ ሙሉ በሙሉ ኃላፊነት ወስደው ሲወያዩበት: ሲከራከሩበት እኔ እነርሱን በአግራሞት እየተመለከትኩ በውስጤ ግን ፍርሃት ሲንሰራፋ ተሰማኝ:: ምክንያቱም የሚያወሩት ነገር ለኔ ባዕድ ሆነብኝ: ምንም የማውቀው ነገር የለም:: በሚቀጥለው ዓመት እኔም እንዲህ እንደነሱ ኢንተርን ስሆን አሁን እንደሚያደርጉት ማድረግ እችል ይሆን? ብየ ራሴን ጠየኩ:: ከባለፈው ሳምንት የፈተና ወቅት ሽብር ወጥቼ ሌላ ሽብር ውስጥ ገባሁ:: ጣጣ ነው:: አራተኛ ዓመት ላይ ያወኩትን በሙሉ ረስቼዋለሁ ማለት ነው......የተመደቡልኝን ህሙማን በሁዋላ ማነጋገርና መመርመር እንዳለብኝ ሳስበው ለራሴ ዘገነነኝ:: ዶክተር ጴጥሮስ ከረዥም ቁመናው: ቀላ ካለው ፊቱና በነጭ ሸሚዙ ላይ ካንጠለጠው ያማረ ከረባት የማልጠብቀው ቁጣና አዘቃዛቂ ስድቦች ያሉት ሰው ነው::  ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ኮሪደሩ ላይ እርሱኑ እየጠበቅን ስናወራ ገና ለመጀመሪያ ግዜ ያገኘን ቢሆንም ሰላም እንኩዋ ሳይለን “What are you guys doing here!?” በማለት በጅምላ ቀልባችንን ገፎ ከቆምንበት በታትኖናል::  በውስጤ ይህችን ሳምንት ከአስተማሪ ወቀሳና ስድብ ልትረፍ እንጂ ለሚቀጥለው ሳምንት አውቅበታለሁ አልኩ::
 ::

Tuesday, July 4, 2017


አርብ ጥቅምት 9  1988 አ.ም.

ዛሬ በተለካሁበት የተግባር ፈተና ሰርጀሪ ትምህርት በሂወቴ ለመጨረሻ ግዜ ተጠናቀቀ:: ስፔዣላይዝ ላለማድረግ የወሰንኩት የህክምና ዘርፍ  ስለሆነ ዳግም  በትምህርት መልኩ የሚገጥመኝ አይመስለኝም:: የጠዋቱ ፈተና አንዲት የእንቅርት በሽታ ተጠቂ የሆንች እንስት ላይ ነበር:: ብዙም ታሪካዊ አልነበረም:: ከሰዓት ግን ፈተናዬን ስጨርስ ደስተኛ አልነበርኩም:: የቃል አንካ-ስላንትያው (VIVA EXAM) አባጣ ጎርባጣ የበዛበት ነበር:: የፈተነኝ በጣም የምወደውና የማከብረው ቀዶ ሀኪም ዶክተር ሚናስ ነበር:: እንዳጋጣሚ ሆኖ ግን ፈተናው ላይ ኮከባችን አልገጠመም:: አመላለሴ አልጣመውም:: ሚናስ የተቆጣ መሰለኝ:: ነብር ሆኖ ታየኝ:: ምንድን ነው ችግሩ? የሱን ሁኔታ በማየት ከፈተናው በፊት የተጨነኩት ሳያንስ ፈተና ውስጥ እያለሁ ጨነቀኝ:: ግራ ተጋባሁ:: ከፈተናው በሁዋላ በውስጤ የነበረው ብቸኛው ተስፋ ይህ ፈተና የውስጥ (Internal) የመሆኑ ሀቅና ከፅሁፍ ፈተናው ጋ ተደምሮ የኔን የቀዶ ሕክምና ችሎታ ለመገምገም የሚኖረው ድርሻ ከሲሶ ያነሰ (30% )ብቻ መሆኑ ነው:: ሌላው 70% የሚመጣው ሙሉ በሙሉ ከመጨረሻው የውጭ የተግባር (External) ፈተና ነው:: ያ ፈተና ገና ብዙ ወራቶች ይቀሩታል:: እዚያ ላይ እበረታ ይሆን በሚል በጭንቅላቴ የተፈጠረችውን አናሳ ተስፋ ሙሉ በሙሉ ጨበጥኩዋት እና ሚናስን ረሳሁት......

ሰኞ ና ማክሰኞ ጥቅምት 5 ና 6  1988 አ.ም.
የፈተናዬ ቀን ሮብ መስሎኝ ተሸብሬ ነበር:: በአይኖቼ መንቀጥቀጥ የታጀበ ጥልቅ ጭንቀትና መደናበር ውስጥ ነበርኩ:: ነገር ግን ዛሬ ሚኪያስ የኔና የርሱ ተራ አርብ መሆኑን ሲነግረኝ ደስ አለኝ::  አርብ ለት ከሚኪያስ ቀጥሎ ሁለተኛው ተፈታኝ ነኝ:: ይህን በማወቄ አሁን መረጋጋት ብቻ ሳይሆን የፈተና ፍራቻዬ ቀንሶ የንባብ አትኩሮቴ ደሞ ጨምሯል:: ሰውነቴ በቅፅበት ተፍታታ:: እጅግ በጣም ተፍታታ::  ነገ ቢሆንስ ኑሮ ፈተናዬ? አርብ በመሆኑ እድለኛ ነኝ አልኩ በውስጤ ...አንዳንድ ያላነበብኩዋቸውን ሀቆች ለመሸፈን ግዜ አገኘሁ ማለት ነው::

ማክሰኞ ለት ምሽት ላይ መብራት ተቁዋርጦ ስለነበር ለፈተና የማደርገው ዝግጅት ተስተጉዋጉሎ ነበር:: አሁንም ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ተኩል ይህን እየፃፍኩ ያለሁት በሻማ መብራት ነው:: እኔ ይህን ፅሁፍ እየፃፍኩ ባለሁበት ቅፅበት የመኝታ ክፍል ተጋሪዎቼ የሆኑት ቤተማርያምና በየበሩ የሻማ ብርሃን ተጠቅመው እያጠኑ ነው:: በየበሩ ማስታወሽ እየፃፍኩ እንደሆነ አውቁዋልና ይህችን የሻማ ንባብ ወቅት እንድከትባት አሳሰበኝ:: በዚህ የፈትና ዋዜማ ከመቼውም ግዜ ይበልጥ የሚፈለገው የኤሌትሪክ ብርሃን ባለመኖሩ እንዴት ፍዳችንን እያየን እንደምናጠና እንድፅፍ አሳሰበኝ:: በዚህ የጭንቅ ሰዓት አጋር ሆና የገኘችው ቀጭኗ ሻማ ምስጋና ይገባታል:: እርስዋ ባትኖርስ ኖሮ? ነገ ሮብ የሰርጀሪ ተግባር ፈተና በይፋ ይጀመራል:: እኔ ቤተማርያምንና በየበሩን ትቼ አስር ሚሊ-ግራም ዲያዘፓም ውጬ ልተኛ ዝግጅቴን አጠናቀኩ......